tg-me.com/kidusan_z_ethiopia/3181
Last Update:
በዓለ ደብረ ታቦር
ክፍል አንድ
ከጌታችን ዓበይት በዓላት አንዱ በየዓመቱ ነሐሴ ፲፫ ቀን የምናከብረው የደብረ ታቦር በዓል ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ብርሃነ መለኮቱን፣ ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት በመሆኑ በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፡፡ (ማቴ .፲፯፡፩፣ ማር.፱፡፩፣ሉቃ.፱፡፳፰)፡፡
ደብረ ታቦር፡- ‹‹ደብረ ታቦር›› ደብር እና ታቦር ከሚባሉ ከሁለት ቃላት የተገኘ ሲሆን ‹‹ደብር›› ማለት ተራራ ማለት ነው፤ ‹‹ታቦር›› ደግሞ በናዝሬት አካባቢ በሰማርያ አውራጃ በገሊላ የሚገኝ የረጅም ተራራ ስም ነው፡፡ የደብረ ታቦር ተራራ ከገሊላ ባሕር በምዕራባዊ በኩል ፲ ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኝ ሲሆን፤ ከፍታው ከባሕር ጠለል በላይ ፭፻፸፪ ሜትር ነው፡፡ በዚህ ተራራ ላይ ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብርሃነ መለኮቱን እንደሚገልጽ ክቡር ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦርና አርሞንኤም በስምህ ደስ ይላቸዋል” በማለት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፡፡ (መዝ. ፹፰፥፲፪) ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ተራራ ላይ ብርሃነ መለኮቱን በመግለጡ የነቢያት ትንቢት ተፈጽሟል፡፡ በዘመነ መሳፍንት ባርቅ ሲሳራን ከነሠራዊቱ ድል ያደረገው በደብረ ታቦር ተራራ ላይ ነበር፡፡ (መሳ. ፬፥፮)፡፡ የዚህም ታሪክ ምሳሌነቱ ባርቅ የጌታችን ሲሳራ ደግሞ የአጋንንት ነው፡፡ ጌታችን በደብረ ታቦር ክብሩን በመግለጥ በአይሁድ እያደረ አምላክነቱን እንዲጠራጠሩ ያደረጋቸውን አጋንንት ድል የማድረጉ ምሳሌ ነው፡፡ በዚህ ተራራ ነቢዩ ሳሙኤል ትንቢት ተናግሮበታል፡፡ ንጉሥ ሳኦልም ከሦስት ሰዎች ጋር ተገኝቶበታል (፩ኛ ሳሙ.፲፡፫)፡፡ ርእሰ አበው አብርሃምና ኖኅ በዚህ ተራራ ላይ ቀስተ ደመና ተተክሎ ያዩ ሲሆን አባታችን ኖኅ ይህንን ተራራ ‹‹መካነ ብርሃን፤ የብርሃን ቦታ›› ብሎ ጠርቶታል፡፡
BY ✞✞✞ በእንተ ቅዱሳን ✞✞✞
Warning: Undefined variable $i in /var/www/tg-me/post.php on line 283
Share with your friend now:
tg-me.com/kidusan_z_ethiopia/3181